1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመድኃኒት እጥረት በአማራ ክልል

ማክሰኞ፣ መስከረም 29 2016

በአማራ ክልል ወቅታዊው የክልሉ የሰላም መደፍረስ በፈጠረው የመንገዶች መዘጋጋት እና መድኃኒቶች በቀላሉ ወደ ጤና ተቋማት መድረስ ባለመቻላቸው ህሙማን ተገቢውን ህክምና እያገኙ እንዳለሆነ የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ። በደምና በኦክስጅን አቅርቦት ችግር ወላዶች ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነም ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/4XMs4
ፎቶ፤ በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የሰሜን ምዕራብ ክላስተር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ባሕር ዳር ቅርንጫፍ
በአማራ ክልል ወቅታዊው የክልሉ የሰላም መደፍረስ በፈጠረው የመንገዶች መዘጋጋት እና መድኃኒቶች በቀላሉ ወደ ጤና ተቋማት መድረስ ባለመቻላቸው ህሙማን ተገቢውን ህክምና እያገኙ እንዳለሆነ የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ። ፎቶ፤ በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የሰሜን ምዕራብ ክላስተር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ባሕር ዳር ቅርንጫፍምስል Alemnew Mekonnen/DW

የመድኃኒት እጥረት በአማራ ክልል

ከሐምሌ 2015 ዓ ም መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልልበተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራቸው ተስተጓጉሏል። ችግር ካጋጣማቸው ተቋማት መካከል የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው የምዕራብ አማራ አካባቢ የጤና ተቋማት ይጠቀሳሉ። በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማ የሚገኙ አንድ ታካሚ ያጋጠማቸውን የመድኃኒት እጥረት ለዶይቼ ቬሌ ሲገልፁ፤ «ኤሌክትሪክ አደጋ ደርሶብኝ ለመታከም ወደ ሆስፒታል ሄጀ ነበር፣ መድኃኒት በሀኪም ቤቱ ባለመኖሩ ከግል መድኃኒት ቤት መድኃኒት በ12 ሺህ ብር ገዝቻለሁ፣ በግል መድኃኒት ቤት ያሉ መድኃኒቶችም እያለቁ ነው።» ብለዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ሆስፒታል ባለሙያ በበኩላቸው በመድኃኒትና በደም እጥረት ምክንት  ህሙማን  በተለይ እናቶች እየሞቱ እንደሆነ ገልፀዋል። እንደ ባለሙያዋ የደምና የኦክስጅን እጥረት በከፋ ሁኔታ በሆስፒታሉ ይስተዋላል። የፍኖተሰላም ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ  አቶ ማናየ ጤናው በስልክ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት በደምና በኦክስጅን አቅርቦት እጥረት በቅርቡ ሁለት ወላዶች ሕይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል። በአካባቢ ከሚገኙ ወረዳዎች በመበደርና በትብብር በመውሰድ የመድኃኒት አገልግሎት ለታማሚዎች ያቀርቡ እንደነበር የገለፁልን በምሥራቅ ጎጃም ዞን የየጁቤ ሆስፒታል ሐኪም፣ አሁን ግን ወረዳዎችም መድኃኒት በመጨረሳቸው ያን ማድረግ እንዳልተቻለ አመልክተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ፣ ድምፃቸውም እንዲቀየር የፈለጉ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ሐኪም የመድኃኒትና የጀነሬተር እጥረቶች፣ እንዲሁም የመብራት መቆራረጥ በተለይ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ፈተና እንደሆነ ተናግረዋል።  እንደባለሙያው አገላለፅ፣ «ያለ መድኃኒት በሆስፒታሉ ውስጥ መሥራት፣ ያለ ጥይት መሳሪያ ይዞ ጦርሜዳ እንደመዋል ነው።»

ፎቶ ከማኅደር፤ ባሕራዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል
በጦርነቱ ምክንያት በሀኪም ቤቶች የመድኃኒት፣ የህክምና ግብአቶች እንደ ደምና ኦክስጅን አቅርቦት ችግር እንዳስከተለ ነው የተነገረው። ፎቶ ከማኅደር፤ ባሕራዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታልምስል DW

የደብረ ማርቆስ የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ ከፋለ ገበየሁ ወቅታዊ ሁኔታው ደም ለመሰብሰብ አላስቻለንም ነው ያሉት። «ደም ለመሰብሰብ ሁለት ዓይነት መንገዶች አሉ፤ አንዱ ጊዜያዊ ድንኳኖችን አቁሞ ከፈቃደኞች ደም መውሰድ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ወደ ደም ባንክ ማዕከሉ የሚመጡ በጎ ፈቃደኞችን መቀበል ነው። ይሁን እንጂ አሁን ያን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም።» በማለት የገጠማቸውን ችግር ተናግረዋል። ናሙናዎችን ወደ ባሕር ዳር ለመውሰድም የመንገዶች በፀጥታ ሁኔታ መዘጋጋት ሌላው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሆነ ገልፀዋል።

የመድኃኒት አቅርቦትን በተመለከተ የጠየቅናቸው፤ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት  የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሳሉ ጫኔ እንደሚሉት የፕሮግራም የሚባሉ መድኃኒቶች ከለጋሽ ድርጅቶች በእርዳታ የሚሰጡ ሲሆን በራሳቸው መሥሪያ ቤት በግዥ የሚፈፀሙ ደግሞ አሉ፣ ሁለቱንም ለማጓጓዝ አውሮፕላን ይጠቀማሉ። ከዚያም መድኃኒቱ ባሕር ዳር ከደረሰ በኋላም አንፃራዋ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች መድኃኒቶቹ እንደሚሰራጩ አስረድተዋል። የመንገድና የፀጥታ ችገሮች እያሉም ሰሞኑነ የተወሰኑ መድኃኒቶችን ወደ ምሥራቅ ጎጃም ማድረስ መቻላቸውን አመልክተዋል። ወደ ምዕራብ ጎጃም አካባቢዎችም ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ሆኖም አሁንም የመንገዶች ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግሩ በተለይም የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው የምዕራብ አማራ በአካባቢዎች ጎልቶ እንደሚታይ ነው ባለሙያዎቹ ያመለከቱት። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ወደ ክልሉ ጤና ቢሮ በአካል ጭምር ሄደን ብንሞክርም «ኃላፊዎቹ ለስልጠና ወደ ሌላ አገር ሄደዋል» በመባሉ ሊሳካልን አልቻለም።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ