1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢ ደረጃ የደረሰው የመንግሥትና ህዝብ ሀብት ምዝበራ

ሐሙስ፣ መጋቢት 28 2015

በደቡብ ክልል በተለያዩ ጊዜያት «በኦዲት ግኝት የተመዘገበ» የተባለ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ እስከአሁን አለመመለሱን የክልሉ የኦዲት የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ኃይል አስታወቀ። በአንዳንድ የክልሉ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች የሚታየው ዳተኝነት ለግኝቱ አለመመለስ ምክንያት መሆኑንም አስመላሽ ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4PmwC
Äthiopien Hawassa, Sidama | SNNPR Finance Bureau
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«በኦዲት ግኝት የተመዘገበ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ አልተመለሰም»

በደቡብ ክልል በተለያዩ ጊዜያት «በኦዲት ግኝት የተመዘገበ» የተባለ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ እስከአሁን አለመመለሱን የክልሉ የኦዲት የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ኃይል አስታወቀ። በአንዳንድ የክልሉ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች የሚታየው ዳተኝነት ለግኝቱ አለመመለስ ምክንያት መሆኑንም አስመላሽ ግብረ ኃይሉ ገልጿል። የቀረበው የኦዲት ግኝት መጠን የክልሉ የፋይናንስ ሥረዓት በአግባቡ እየተመራ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ለዶቼ ቬለ DW አስተያታቸውን የሰጡ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በበኩላቸው ተጠያቂነት በሌለበት ግኝት ብቻውን መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ በመንግሥት እና በህዝብ ሀብት ላይ የሚስተዋለው ምዝበራ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ መድረኮች ሳይገለጽ ያለፈበት ጊዜ ያለም። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ አህመድም ከወራት በፊት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ ማስገባታቸው ይታወቃል። በሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ችግሮች ከሚስተዋሉባቸው ክልሎች አንዱ የሆነው የደቡብ ክልል በተለያዩ አካላት እጅ የሚገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው የጥሬ ገንዘብ ሀብት ለማስመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል። ምክር ቤቱ የማስመለስ ሂደቱን ገቢራዊ ለማድረግ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የኦዲት ግኝት አሥመላሽ ግብረ ኃይል በማቋቋም እየሠራ እንደሚገኝ በክልሉ ምክር ቤት የበጀት፤ፋይናንስና የመንግሥት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል። ነገር ግን እስካሁን በጉድለት ተመዝግቦ የሚገኘውን የመንግሥት ሀብትና ንብረት በታሰበው ልክ ማስመለስ አለመቻሉን ነው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበባየሁ ኤርሚያስ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።

የክልሉ የ2014 ዓም የኦዲት ግኝት የብር 19 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተሰብሳቢ ገንዘብ መኖሩን እንደሚያሳይ የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበባየሁ «ይህ ቀላል የሚባል ሀብት አይደለም። በተለያዩ የዞን እና የወረዳ መዋቅሮች ውስጥ በሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ የሚገኝ ነው። ይህ ሀብት ከእያንዳንዱ ተቋምም ሆነ ግለሰብ መመለስ ይኖርበታል። አሁን ምንም እንኳን በሚጠበቀው ደረጃ ባይሆንም ክልሉ የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ኃይል በማቋቋም እየሠራ ይገኛል» ብለዋል።

የባለሥልጣናት ዳተኝነት  

በደቡብ ክልል በኦዲት ግኝት የተለየውን የብር 19, 9 ቢሊየን ብር ተሰብሳቢ ገንዘብ ለማስመለስ የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትን ያካተተ የኦዲት ግኝት አሥመላሽ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ በሥራ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ የማስመለስ ሥራው ለተቋቋመው ግብረ ኃይል አልጋ በአልጋ የሆነለት አይመስልም። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ የግብረ ኃይሉ ባለድርሻ አካካት የተለያዩ ምክንያቶችን ያነሳሉ። አቶ አበራ ኪጴ   የኦዲት ግኝት አሥመላሽ ግብረ ኃይል አባል የሆነው የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ናቸው። አሁን በክልሉ በተወሰኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች አማካኝነት እየባከነ የሚገኘው  የገንዘብ ሀብት ቀላል አይደለም የሚሉት አቶ አበራ «እኛ በግምገማችን  ያረጋገጥነው በጉዳዩ ላይ የአመራር እጅ እንዳለበት ነው። ምክንያቱም ሀብቱን ለማስመለስ አመራሩ ቁርጠኝነት አይታይበትም። ይልቁንም ጉዳዩን ዝም ብሎ የማንከባለል ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። ለዚህ ደግም ዋናው ምክንያት አንዳንድ አመራሮች በሂደቱ ውስጥ ንክኪ ሥላላቸው ነው።  ይህን ሁኔታ ለመቀልበስ አሁን በትኩረት መሰራት እንዳለበት በመተማመን ወደ ተግባር ገብተናል» ብለዋል።

Äthiopien Währung Birr
ምስል Eshete Bekele/DW

የግኝቱ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ እንድምታ  

ዶክተር ደገላ ኤርጌኖ የደቡብ ክልልን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በቅርበት ከሚከታተሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው።፡ ዶክተር ደገላ ቀደምሲል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አሁን ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት መምህርነትና ተመራማሪነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በደቡብ ክልል ተለየ የተባለውን የ19,9 ቢሊየን ብር የኦዲት ግኝት አስመልክቶ ዶቼ ቬለ DW አስተያየታቸውን የጠየቃቸው  ዶክተር ደገላ «ግኝቱ በጣም ትልቅ ሊባል የሚችል ነው። ከሁሉ በላይ ግን  የክልሉ የፋይናንስ ሥረዓት በአግባቡ እየተመራ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው» ብለዋል።

የተጠቀሰ ግኝት በክልሉ ሊያሳድር የሚችለው ምጣኔ ሀብታዊም ሆነ  ፖለቲካው ተፅኖው ቀላል አይደለም የሚሉት ዶክተር ደገላ «ዋናው ተፅኖ ክልሉ በበጀት ሥረዓትን ተከትሎ እየሄደ ባለመሆኑ ወጭውን በገቢው እንዳይሸፍን ሊደርገው ይችላል። ይህ ደግሞ አይደልም አንገብጋቢ የድህንት ቅነሳ ሥራዎችን ለማከናወን ቀርቶ ክልሉ ለቀጠራቸው ሠራተኞችም ደሞዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ሊያደርሰው ይችላል» በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

በግኝት የተገኘው የገንዘብ ሀብት በአብዛኛው ከግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ የተሰበሰብ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ደገላ «በዚህ ግኝት ምክንያት ግብር እየከፈሉ ልማት ያላገኙ ዜጎችን ቅሬታ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። ይህም መጨረሻ ላይ በአስፈጻሚው አካል ላይ ተጨማሪ ፖለቲካዊ ተፅኖ የማሳደር ሠፊ ዕድል አለው» ብለዋል።

የተጠያቂነት ጉዳይ  

በደቡብ ክልለ በግኝት የተለየውን የገንዘብ ሀብት ለማስመለስ ሁለት ተግባራትን በመፍትሄነት መፈጸም ይገባል ይላሉ፤  የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪው ዶክተር ደገላ። በፋይናንስ አሠራር ረገድ ወጥ የሆነና የመንግሥትን የበጀት አሠራር በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የመጀመሪው እርምጃ ሊሆን እንደሚገባ የጠቀሱት ዶክተር ደገላ አስፈጻሚው አካል ለዚህ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

ክልሉን ወደ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለማስገባት የበጀት ሥረዓቱን በኦዲት ምርመር ከመቆጣጠር ጎን ለጎን የክልሉ መንግሥት ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኑ እንዳለበት የተናገሩት የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪው « የተጠያቂነት አሠራር ካልሰፈነ ግኝት ብቻውን መፍትሄ ሊያመጣ ሥለማይችል አስፈጻሚው አካል በዚህ ረገድ በሥፋት ሊሠራ ይገባል» ብለዋል። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶ ስለሺ