1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የኢጋድ የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ሐሙስ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ላይ ይመክራል

Eshete Bekele
ዓርብ፣ ጥር 3 2016

ስለ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ለመወያየት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ጠርቷል። የኢጋድን ጥሪ ካከበሩ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” ከተፈረመ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ የሚገናኙበት የመጀመሪያ መድረክ ይሆናል

https://p.dw.com/p/4bAmV
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ እና የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ
የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች በመጪው ሐሙስ በዩጋንዳ በሚያደርጉት አስቸኳይ ጉባኤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ላይ ይወያያሉምስል Ethiopian PM Office

የኢጋድ የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ሐሙስ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ላይ ይመክራል

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት የወቅቱ ሊቀ-መንበር የጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ውዝግብ ላይ ለመምከር የአባል ሀገራት መሪዎችን ለአስቸኳይ ጉባኤ ጠርተዋል። በዩጋንዳ የሚካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመሯቸው ኃይሎች ለዘጠኝ ወራት ውጊያ የገጠሙባት የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ጭምር ይወያያል።

ጥሪውን ካከበሩ ጥር 9 ቀን 2016 የሚካሔደው የኢጋድ አስቸኳይ ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” ከተፈረመ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ የሚገናኙበት የመጀመሪያ መድረክ ይሆናል። የመግባቢያ ሥምምነቱ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ከተፈረመ ወዲህ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት ውዝግብ ተጭኖታል።

የዐቢይ መንግሥት ዓለም አቀፍ እውቅና አጥብቃ ከምትሻው ሶማሌላንድ የመግባቢያ ሥምምነቱን የተፈራረመው በበርካታ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች በተወጠረበት ወቅት ነው። “የኢትዮጵያ ውስጠ-ፖለቲካ በብዙ መልኩ የተረጋጋ አይደለም” የሚሉት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ሙከርም ሚፍታህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የተከተለው መንገድ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው የሚለው ትችት “በከፊልም ቢሆን ትርጉም” የሚሰጥ እንደሆነ ይናገራሉ።   

ዶክተር ሙከርም “መንግሥት በዚህ በኩል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫውን እንደ አዲስ አጀንዳ ቀርጾ የሀገር ውስጥ ፖለቲከኛውም፣ ምሁሩም በቀጠናው ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ተንታኙም እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሀገሮችም በዚያ እንዲጠመዱ በማድረግ [ትኩረቱን] ከውስጠ-ፖለቲካው ዘወር ለማድረግ የተኬደበት ነው የሚለው በከፊልም ቢሆን ትርጉም ያለው ይመስላል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

 የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ
የስምንቱን የኢጋድ አባል ሀገራት ለአስቸኳይ ጉባኤ የጠሩት የክፍለ አኅጉራዊው ድርጅት የወቅቱ ሊቀመንበር የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ ናቸው። ምስል Reuters

የመግባቢያ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ሊከበር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሁለቱ ሀገሮች ልዩነቶቻቸውን በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክን የመሳሰሉ ሀገራት የሰጧቸው መግለጫዎችም ተመሳሳይ ቃና ያላቸው ናቸው።

የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና አንድነት እንዲከበር ጥሪ የሚያቀርቡት መግለጫዎች “በግልጽ ቋንቋ” የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመውን የመግባቢያ ሥምምነት የተቹ አለመሆናቸውን ዶክተር ሙከርም ይናገራሉ። “የኢትዮጵያን መንግሥት ማስከፋት አይፈልጉም። ግን ደግሞ ግልጽ ወጥተው ማበረታታት አልፈጉም” ሲሉ አስረድተዋል።

“የሞቃዲሾ መንግሥት ዓለምን አደራጅቶ ይኸ ነገር እንዲጨናገፍ የሚያደርገው ጥረት ብዙ ርቀት የሚሔድ አይመስለኝም” የሚሉት ዶክተር ሙከርም ይልቁን ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ምን ያክል ተዘጋጅተውበታል የሚለው ጉዳይ በአጽንዖት የሚያነሱት ነው።

“በሶማሌላንድ እና በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የዓለምን የፖለቲካ ኃይሎች የትኩረት አቅጣጫ ከማስቀየስ ባሻገር ጥያቄው የልማት ጥያቄ የኅልውና ጥያቄ ሆኖ ወደ ሌላ ሁለተኛ ምዕራፍ አልፎ፣ ወደ ፕሮግራም ተቀይሮ፣ በጀት ተመድቦበት ሥራ ወደሚሰራበት ምዕራፍ ይወስዱታል? አይወስዱትም?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ
በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የመግባቢያ ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ መክረዋል። ምስል Feisal Omar/REUTERS

 የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ያደረጉት ውይይት፤ እና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜሕ ሽኩሪ የአስመራ ጉዞ ግን ዲፕሎማሲያዊው ቁርቁስ ወዴት ሊሔድ ይችላል የሚል ጥያቄ የሚያጭሩ ናቸው። ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ በግብጹ አቻቸው አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ ወደ ካይሮ ተጋብዘዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማሸማገል እስካሁን ድረስ በይፋ ጥያቄ ያቀረበ ወገን የለም። ዶክተር ሙከርም ግን ልዕለ ኃያላኑም ሆኑ በቀጠናው ጥቅም ያላቸው ቱርክ እና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት ውዝግቡ ወደ ግጭት እንዳያመራ የሚያደርግ መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ የሚል ዕምነት አላቸው። 

“ሁለቱ ኃይሎች ብዙ ሳይጋጩ ውስን ፍጭት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ጉዳዩ እንዲቀጥል ነው የሚሆነው” የሚሉት ዶክተር ሙከርም  “ነገር ግን የሶማሊያ መንግሥት በጣም ተጠቂ እንዳይሆን አደጋን የመቀነስ፤ በሐሳብ፣ በቃላት እና በዲፕሎማሲ ደረጃ ያለውን ቁርቁስ የማለዘብ፤ ወደ መሣሪያ እና ወደ ማዕቀብ እንዳይሸጋገር ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ እገምታለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስለ የመግባቢያ ሥምምነቱ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው ማብራሪያዎች ብዙ ጥቅም እንደሚገኝ ተስፋ የሚሰጡ ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ጉዳዩን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ከተፈጠረ ጫና አወዳድረውታል።

“የሥጋት ከበሮ እየተደለቀ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በምድርም በአየርም ልምምድ” እያስገመገመ የግድቡ ግንባታ መከናወኑን የጠቀሱት ሬድዋን “የባህር በሩም እንዲሁ ይሆናል” ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ